Phone: 011 552 4395 / 011 552 2331 E-mail: registrar@ptcethiopia.com 

“እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ” ማቴ. 6፥9 የትና እንዴት እንጸልይ ከሚለው ይልቅ ወደ ማን እንጸለይ የሚለው ጥያቄ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። እንዴት እንደምንጸልይ ተምረን ነገር ግን የምንጸልየው ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ወይም አድራሻ ከሆነ መማራችን ከንቱ ይሆናል። ሆኖም እንዴት እንጸልይ የሚለውን ጥያቄ የት እንጸልይ ከሚለው የበለጠ አስፈላጊ ነው። በትክክለኛው አድራሻ እና በተገቢው መንገድ ከጸለይን ቤት ውስጥ ሆነንም ቢሆን እየሄድን፣ ወይም ደግሞ በሥራ ላይ ሆነን ብንጸልይ ምንም ልዩነት የለውም። በውስጣችን ያለው ከእኛ ውጪ ካለው ነገር ይልቅ በጣም አስፈላጊ ነው። ስለዚህ በዚህ ክፍለ ትምህርት ስለ እውነተኛው አምላክና ወደ እርሱም እንዴት እንደምንጸልይ እንነጋገራለን። እንደፈቃዱ መጸለይ እንድንችል ስለ እግዚአብሔር በጣም አስፈላጊ ስለሆኑ ነገሮች እናጠናለን። በጸሎታችን ወቅት የምንናገረው ነገር የሕይወት ጉዞአችንን እንዴት ሊነካው እንደሚችል እንመለከታለን፡፡ ብዙ የምንማራቸው ነገሮች ይኖሩናል። የክፍለ ትምህርቱ አከፋፈል • ስለ እግዚአብሔር የተሳሳቱ እሳቤዎች • ራሱን የሚገልጥ አምላክ • ስለ ጸሎት የክርስቶስ ትምህርት የክፍለ ትምህርቱ ዓላማዎች ይህንን ክፍለ ትምህርት ስታጠናቅቅ የሚከተሉትን ማድረግ መቻል ይኖርብሃል። • ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ያላቸውን የተሳሳተ አመለካከት መረዳት ይህም አመለካከት እንዴት አምልኳቸው ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር መወያየት፤ • እውነተኛው አምላክ ራሱን የገለጠባቸው መንገዶች መለየት፤ • ኢየሱስ ስለ ጸሎት ያስተማረውን ማጠቃለልና መመሪያዎችን በሕይወት መተግበር ናቸው። የክፍለ ትምህርቱ መመሪያዎች 1. በማቴ. 6፥5-8 ያሉትን ጥቅሶች በሙሉ በቃልህ አጥና። 2. የትምህርቱን ማጠናከሪያ ክፍል በክፍል አንብብ። በእያንዳንዱ ክፍል ያሉትን የጥናት ጥያቄዎች መልሶችን ጻፉ። በዚህ ክፍለ ትምህርት ውስጥ አንዳንድ የጥናት ጥያቄዎች በምርጫ መልክ ቀርበዋል፤ ትክክለኛውን መልስ ለማመልከት፣ መልስ ይሆናል ብለህ የምታስበውን ፊደል ክበብ። 3. በክፍለ ትምህርቱ መጨረሻ ላይ የሚገኘውን የሙከራ ፈተና ሥራና የሰጠኸውን መልስ በመጽሐፉ መጨረሻ ላይ ከምታገኘው መልስ ጋር አስተያይ። በቃል እንድታጠናቸው ከተሰጡህ ጥቅሶች ውጭ ያሉ ጥቅሶችን ለመመልከት መጽሐፍ ቅዱስህን መመልከት ትችላለህ። 4. የትምህርት ማጠናከሪያውን እንደጨረስህ ወደ ትምህርቱ ዓላማ ተመለስና እንድታደርግ የተጠየከውን መፈጸምህን አረጋግጥ። 5. ማስታወሻ ደብተር በማዘጋጀት በጥናት ጥያቄዎች ላይ ሰፋ ያሉ መልሶችን ለመጻፍ ተጠቀምበት። አዳዲስ ቃሎችና አሳቦችም ካጋጠሙህ በማስታወሻው ላይ ጻፋቸው። ትምህርቱ ዝርዝር ስለ እግዚአብሔር የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ዓላማ 1 ስለ እግዚአብሔር የተሳሳቱ ሰባት ዕሳቤዎችን ማብራራት። “እግዚአብሔር የለም” ባዩ ሰው ስለ ጸሎትና አምልኮ ማጥናት ስንጀምር ሰዎች ወደ እርሱ የሚጸለዩለት አንድ አምላክ ወይም አንድ ነገር መኖር አለበት በማለት እንጀምር። የሚመለክ ከሌለ ማምለክ አትችሉም። አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሔር የለም፣ ስለዚህ ሊመለክ የሚገባው ነገር የለም፤ የሚሰማም ስለሌለ መጸለዩ ዋጋ የለውም ይላሉ። እነዚህን ሰዎች “አምላክ የለሾች” በእንግሊዝኛ ደግሞ ኤቲስት ብለን እንጠራቸዋለን። ምክንያቱም በእግዚአብሔር ህልውና አያምኑም። ሞኞችም በመሆናቸው ስለ እግዚአብሔር ህልውና ማረጋገጫ ሆኖ በዓይና ቸው ፊት የተቀመጠውን እንኳን ማየት አይችሉም። ያለ አንዳች መዛባት በስርዓት የሚጓዘው ዓለም፣ የአበቦች ውበት፣ አስደናቂው አካላችን፣ ሁሉም ነገር በአንድ ድምጽ “ፈጣሪ አምላክ አለ” ብሎ ያስተጋባል። ዓለማችን ያለ ፈጣሪ እንዲሁ ተገኘች ብሎ ማሰብ አንድ የእጅ ሰዓት እንዲሁ ያለ ሠሪ ተገኘ ብሎ እንደማሰብ ነው። ለሚከተለው ጥያቄ ተስማሚውን መልስ በመምረጥ ክበብ። (1). አምላክ የለሽ አይጸልይም ምክንያቱም ሀ. እግዚአብሔር ስለመኖሩ አያምንም። ለ. እግዚአብሔር ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለም። ሐ. እግዚአብሔርን መታዘዝ አይፈልግም። “እርግጠኛ መሆን አይቻልም” ባዩ ሰው አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሔርን ስለማያዩት ይቸገራሉ። ፍጥረቱን ሁሉ ያዩና ለእነዚህ ሁሉ ፍጥረታት መገኘት ምክንያት የሆነ አንድ ነገር መኖሩን ያምናሉ። ነገር ግን በመጠራጠር እርግጠኛ መሆን አይቻልም፤ ይህንን የፈጠረ እግዚአብሔር ሊሆንም ላይሆንም ይችላል ይላሉ። እነዚህን ሰዎች ተጠራጣ ሪዎች፣ በእንግሊዝኛም አግኖስቲክስ ብለን እንጠራቸዋለን፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ህልውና ባይክዱም ሰው ስለ እርሱ ማወቅ አይችልም የሚል አቋም አላቸው። ስለዚህም የሚሰማህ ከሌለ ለምን ትጸልያለህ? ብለው ይጠይቃሉ። “እግዚአብሔር አያስፈልገኝም” ባዩ ሰው የእግዚአብሔርን መኖር የሚገነዘቡ እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ፤ ነገር ግን ሊታዘዙት አይፈልጉም። እነዚህ ሰዎች የሚያውቁትን እውነት መቀበል የማይፈልጉ በመሆናቸው “የማይታዘዙ” እንላቸዋለን። ለእውነት ስለማይ ታዘዙ አይጸልዩም፤ ምክንያቱም “ሰዎች ሥራቸው ክፉ ስለ ነበረ፣ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ” (ዮሐ. 3፥19)። ነገር ግን ለእውነት የማይታዘዙ ሰዎች የሚጸለዩበት ቀን ይመጣል። ተራሮችና ዓለቶች እንዲወድቁባቸውና በዙፋ ኑም ከተቀመጠው ፊት እንዲሰውሯቸው ይለምናሉ፤ ያ ቀንም የፍርድና የቁጣ ቀን ይሆናል (ራእ. 6፥16) ። (2). ለእውነት የማይታዘዙ ሰዎች ለምን አይጸልዩም? “ተፈጥሮ አምላክ ነው” ባዩ ሰው እግዚአብሔር እና ፍጥረት አንድ ናቸው ብለው የሚያምኑ ብዙ ሰዎች አሉ። ከፍጥረቱ የተለየ ፈጣሪ አምላክ መኖሩን አያምኑም። በእንግሊዝኛ ፓንቴይስት የሚባሉት እነዚህ ሰዎች ዛፎች አምላክ ናቸው፣ ደመናት አምላክ ናቸው፣ ሰው አምላክ ነው . . . ወዘተ ይላሉ። እንዴት ዓይነት ትልቅ ስህተት ነው! ለእነርሱ ተፈጥሮ አምላክ ነው፤ የእነርሱ አምላክ ስሜት የለውም። መልክ የለውም። ጆሮ ስለሌለው ወደ እርሱ መጸለይ አትችልም። ድምጽም ስለሌለው አይመልስህም። ዓይንም ስለሌለው አያይህም። ልብም ስለሌለው አይወድህም። እንዲህ ዓይነቱ አምላክ ምን ዓይነት አምላክ ነው? አየህ እግዚአብሔር ፍቅር ነው ማለትና ፍቅር እግዚአብሔር ነው ማለት ፈጽሞ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። እንዲሁም እግዚአብሔር በፍጥረቱ ይገለጣል ማለትና ፍጥረት እግዚአብሔር ነው ማለት በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው። (3). የ“ተፈጥሮ አምላክ ነው” ባዮች አምላክ የማይፈጽማቸውን አራት ነገሮች ጥቀሱ። “እኔ አምላክ ነኝ” ባዩ ሰው እያንዳንዱ ሰው ደስ በሚለው ነገር የማመን መብት አለው። እንዲሁም የአንዱ ሰው አስተሳሰብ የሌላውን ሰው ያህል ትክክል ነው የሚሉ ሰዎች ያጋጥሟችኋል። እነዚህንም “ራስ አምላኪዎች” በእንግሊዝኛ ኤጐቲስትስ ልንላቸው እንችላለን፤ ምክንያቱም ከራሳቸው በስተቀር ምንም አምላክ አያውቁምና። ምን ማድረግ እንዳለባቸው ከራሳቸው በቀር የማንንም ኃሳብ አይቀበሉም። ራስ አምላኪዎች እነርሱ ያልጣማቸውን የሥነ ምግባር መለኪያ አይቀበሉም። ለእነርሱ መልካም የሆነ ያ ለእነርሱ መልካም ነው። እነዚህ ሰዎች አይጸልዩም። ለምንስ ይጸልያሉ? ከራሳቸው ኃሳብ በቀር የበላይ ባለሥልጣን ወይም መልካምና ክፉ የሚባል ነገር አይፈልጉም። (4). የራስ አምላኪዎች “ኤጐቲስትስ” የሥነ ምግባር መለኪያ ምንድን ነው? “ማንኛውም አማልክት አምላክ ነው” ባዩ ሰው እንዲህ ዓይነት ሰዎች በርካታ ናቸው። ለእነዚህ ሰዎች የትኛውንም አምላክ ማምለክ ምንም ለውጥ የለውም። ይህኛው አምላክ የሌላውን ያህል ጥሩ ነው። ማንኛውም አምላክ ይሠራል ይላሉ። እንደዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች “ሁሉን አምላኪ” በእንግሊዝኛ ደግሞ ዩኒቨርሳሊስትስ ይባላሉ። ሃይማኖቶች ሁሉ ወደ ተራራ ጫፍ እንደሚያወጡ መንገዶች ናቸው ብለው ያምናሉ። እያንዳ ንዱ ሃይማኖት በተለያየ ጎዳና ሄዶ እዚያው ጫፍ ያደርሳል የሚል እምነት አላቸው። ይህ ዓይነቱ ትምህርት አደገኛና ክፉ ነው። እነዚህ ሰዎች እግዚአብ ሔር በሰዎች አእምሮ ውስጥ የተቀረጸ አስተሳሰብ እንጂ በእርግጥ ህልውና ያለው አምላክ አይደለም በማለት ይናገራሉ። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር በሰዎች አእምሮ የተቀረጸ አሳብ ሳይሆን እርግጠኛ ህልውና ያለው ነው። እርሱ ዓለምንና በውስጧ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አንድ አምላክ ነው። እርሱ ማን እንደሆነ እርግጠኛውን ነገር ልናውቅና ልናመልከው ይገባናል። በሚቀጥለው ክፍል እርሱ ማን እንደሆነ እንነጋገራለን። ወደዚያ ከማለፋችን በፊት ግን በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ስለያዙት ስለሌላው እምነት እንነጋገር። (5). ማንኛውም አማልክት አምላኩ የሆነለትን ሰው በእንግሊዝኛ ምን ብለን እንጠራዋለን? የሙታን መንፈስ አምላኪ ሰው በጣም ብዙ ሰዎች ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ ያምናሉ። የሞቱ ሰዎች ከተለዩን በኋላ ደግመው ስለማይታዩ የእነርሱ ነገር ምስጢራዊ ነው። ሙታን አስቀድሞ ይኖሩ ወደ ነበሩበት ሥፍራ በመንፈስ በመመለስ ይንቀሳቀሳሉ ብለው የሚያምኑ ሰዎች አሉ። እነዚህ የሙታን መናፍስት በሕይወት ያሉ ሰዎች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ ድርሻ አላቸው ብለው ያምናሉ። ይህ ዓይነቱ እምነት “የመናፍስት አምልኮ” በእንግሊዝኛ አኒሚዝም ይባላል። በማይታወቀው ነገር እና በማይታየው ነገር ከመጨነቅ የተነሳ በመናፍስት አምላኪዎች ውስጥ ትልቅ ፍርሃት አለ። ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹ አንድ እውነተኛ አምላክ እንዳለ የሚያምኑ ቢሆንም እርሱ ግን ከእነርሱ በጣም የራቀና በችግራቸውም ሊረዳቸው የማይፈልግ ግዴለሽ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ስለዚህ በቅርባችን አሉ ብለው የሚያስቧቸውን የሙታን መናፍስት ለማስደሰት አምልኳቸውንና ጸሎታቸውን በስጦታ በማቅረብ ከመናፍስቱ ሞገስ ለማግኘት ይሞክራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ፍርሃት ቅጣት አለውና” ይላል (1ኛ ዮሐ. 4፥18)። የሙታን መንፈስ አምላኪዎች ስሜት ይህ ነው። እዚሁ ላይ “ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል” ይላል። ከዚህ በኋላ ስሙን ለሚጠሩ ሁሉ ቅርብ ስለሆነው ስለ እውነተኛው የፍቅር አምላክ እንነጋገራ ለን። እርሱ ጸሎትን ለመመለስና ፍርሃትን ለማስወገድ ስልጣን አለው። (6). “የሙታን መንፈስ አምላኪው” ሰው (አኒሚስት) ለምን አስማትንና መሥዋዕትን ይጠቀማል? ራሱን የሚገልጥ አምላክ ዓላማ 2፡- እውነተኛው አምላክ ራሱን የገለጠበትን መንገዶች መገንዘብ። በተጻፈው ቃሉ የተገለጠ ሰው እንዲያመልከውና ወደ እርሱ እንዲጸልይ የሚፈልግ አምላክ ራሱን ለሰው መግለጽ አለበት። እውነተኛው አምላክ እግዚአብሔር፣ ያደረገው ይህንኑ ነው። ራሱን ገለጠ፤ በዚህም እርሱንም ሆነ ፈቃዱን ልናውቅ እንችላለን። እያንዳንዱ ሃይማኖት፣ ወደ ነቢያቶቹ፣ ወደ ራዕዮቹ፣ ወደ ተዓምራቱና መምህ ራኖቻቸው ወደ ሰጡዋቸው ጽሑፎች ያመለክታሉ። እውነተኛው አምላክ ግን እነዚህን ሁሉ ሰጥቶናል። ራሱን ለመግለጥ ከዚህ የሚበልጥም ነገር አድርጓል። ራሱንና ፈቃዱን በሦስት መንገዶች በመግለጽ ተናገረን። እግዚአብሔር ቃሉን በጻፉት በነብያቱ እና በሐዋርያቱ፣ በቅዱሳት መጻሕፍቱ በኩል ራሱን ገልጿል። መጻሕፍቱን በአንድ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ተብለው ይጠራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን አምነው የተቀበሉ ሰዎች ተለውጠዋል። ሰው የኢየሱስን ትምህርት ሲቀበልና የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ሲያምን በዚያ ሰው ሕይወት ውስጥ ተዓምራት ይፈጸማል፤ አዲስም ሰው ይሆናል። ቀድሞ መልካም ነው ብሎ ሲከተለው የነበረውን የክፋት መንገድ ይተዋል። በብዙ ሰዎች፣ በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች የተጻፉትን የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክቶችን ስትመለከቱ፣ ደግሞም ይህንን መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥፋትና ዋጋ ለማሳጣት የተደረገውን ሙከራ ስታዩ፣ ያለ ጥርጥር መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ለእኛ የገለጸልን ተዓምረኛ መጽሐፍ እንደሆነ ትረዳላችሁ። (7). በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ቃሉ እንዲሰፍር እግዚአብሔር የተጠቀመባቸው የትኞቹን ሰዎች ነው? በህያው ልጁ የተገለጠ እግዚአብሔር ራሱን በልጁ በኢየሱስ በኩል ገልጿል። ኢየሱስ እንደ ሰው በዚህ ምድር ላይ ከ30 ዓመታት በላይ ኖሯል። “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተሞልቶ በእኛ አደረ” (ዮሐ. 1፥14)። ኢየሱስ ስለ ራሱ ያለውን አስቡ። የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ተናግሯል። ይህንንም አባባሉን ለማረጋገጥ የፈውስና የሃይል ተዓምራታዊ አገልግሎቱን ፈጽሟል። የኢየሱስን ሞትና ትንሳኤ አስቡ፤ በእርግጥም እግዚአብሔር ራሱን በእርሱ በኩል ገልጿል። በምድር በኢየሱስ አካላዊ መገለጥ በኩል ራሱን ገልጿል። (8). እግዚአብሔር ራሱን የገለጸበት ቃል የተባለው ማን ነው? በመንፈስ ቅዱስ የተገለጠ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነት የሆነውን ለሚቀበል ለማንኛውም ሰው እግዚ አብሔር ራሱን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በማንኛውም ጊዜ ይገልጥለታል። “የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል” (ሮሜ 8፥16)። የእግዚአብሔር መንፈስ የሚያምነውን ሁሉ አዲስ ሰው ያደርገዋል። እምነትህን በእርሱ ላይ ብታደርግ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ራሱን ይገልጥልሃል። እውነተኛውን አምላክ አምልክ ጸልይና የእግዚአብሔር መንፈስ ለመንፈስህ እንዲመሰክር ፍቀድለት። በሕይወትህ የእርሱ ኃይል ከተሰማህ ከዚህ የበለጠ ሌላ ማረጋገጫ አያስፈልግም። እውነተኛው አምላክ ማን እንደሆነም ታውቃለህ። (9). ልጁ ስለሆንክ እግዚአብሔር ራሱን ለአንተ እንዲታወቅ ያደረገበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው? ስለ ጸሎት የክርስቶስ ትምህርት ዓላማ 3 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ባስተማራቸው ጸሎት ውስጥ ቅድሚያ የተሰጣቸውን ጉዳዮች ማብራራት። ስውርና ቀላል ጸሎት ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን “ጌታ ሆይ. . . እንጸልይ ዘንድ አስተምረን” አሉት (ሉቃ. 11፥1)። በትክክል ከሚጸልየው ከጌታ ትክክለኛውን ጸሎት መማር እንችላለን። ስለዚህ ኢየሱስ የጸሎት አስተማሪያችን እንዲሆን እንፍቀድለት። ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱ እንደ ፈሪሳውያን እንዳይጸልዩ ነገራቸው (ማቴ. 6፥5)። ፈሪሳውያን በምኩራቦችና በመንገድ ዳር ይጸልያሉ። በጉባኤ መጸለይ ስህተት ይሆንን? አይደለም። ኢየሱስ ፈሪሳውያንን የገሰጻቸው በጉባኤ መካከል መጸለይ ስህተት ስለሆነ አይደለም። እርሱም ቢሆን በጉባኤ መካከል ጸልዮአል። ስህተት የሚሆነው ግን ሰዎች እንዲያዩልን ተብሎ ሲደረግ ነው። (10). ማቴ. 6፥5-6 ከመጽሐፍ ቅዱስህ ተመልከት። በስውር ለሚጸልዩ እግዚ አብሔር ምን ያደርጋል? አንድ ሰው በርከት ላሉ ሰዎች በጉባኤ ጸሎት ላይ መናገር የሚኖርበት ተገቢና አስፈላጊ የሆኑ ብዙ ነገሮች ይኖራሉ። የሰው ሁሉ ስሜትና አሳብ ጸሎት በሚያደርገው በአንዱ ሰው ላይ ስለሚሆን ምናልባት የጸሎቱ ጊዜ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል። ብዙ ጊዜ ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ከማሰብ ይልቅ ጸሎት ስለሚያደርገው ሰው ያስባሉ። ስለዚህ ይህ ጊዜ ለጸሎት አድራጊው ሰው ከባድ የፈተና ወቅት ይሆናል። ምናልባትም ፈሪሳውያን እንዳደረጉት ሰዎች እንዲያዩትና እንዲሰሙት ሲል ለመጸለይ ይፈተን ይሆናል። (11). ትክክለኛውን መልስ መርጠህ ክበብ። ጌታ ደቀ መዛሙርቱን እንደ ፈሪሳውያን እንዳይሆኑ ነገራቸው። ምክንያቱም ፈሪሳውያን የሚጸልዩት፡- ሀ. በጉባኤ ስለሆነ ለ. ረጅም ጸሎት ስለሚጸልዩ ሐ. ሰዎች እንዲያዩላቸው ብለው ስለሚጸልዩ ነው። ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር ፊት ማምጣት የሚችሉ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የሰዎችን አእምሮና አሳብ ወደ እግዚአብሔር የማቅናት ችሎታ አላቸው፡፡ እኛም ቢሆን የሚያስፈልጉን እንደነዚህ ዓይነት የጸሎት መሪዎች ናቸው፡፡ በተለይ አገልጋዮች ይህን ስጦታ ማዳበር አለባቸው፡፡ ስለራሳችንም ሆነ ስለሌሎች ሰዎች ሳናስብ እንዴት አድርገን ነው ጉባኤውን በጸሎት መምራት ለመማር የምንችለው? ይህንን በጉባኤ ሳይሆን መለማመድ የምንችለው በግል ጸሎታችን ወቅት ነው። እንዲሁም ብቻችንን ከእግዚአ ብሔር ጋር ስንሆን መንፈስ ቅዱስ ከጌታ በቀር ሁሉን ነገር ከአእምሮአችን ማውጣትን ያስተምረናል። ከዚያ በጉባኤ ስንቆም አሁንም በግል የጸሎት ስፍራችን ያለን ያህል ይሰማና። ምንም እንኳን ሰዎች እንደሚሰሙን ብናውቅም አሳባችን ሁሉ የሚያርፈው ለኢየሱስ በምንለው ነገር ላይ ብቻ ነው። በሰዎች መካከል ሆነን ከእግዚአብሔር ጋር ብቻችንን ነን። (12). በጉባኤ መካከል መጸለይን እንዴት መማር እንችላለን? በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ ሰዎች ብዙ ጊዜ አንድ ላይ ይጸልያሉ። ይህም እያንዳንዱ አማኝ ምንም እንኳን ከሌሎች ጋር ቢሆንም ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝበት መንገድ ነው። ሰዎች በአንድ ላይ መጸለያቸው፣ መልካም ልምምድ ነው። ብዙውን ጊዜ፣ በአንድ ላይ ተሰብስበው ሲጸልዩ የእግዚ አብሔር መንፈስ በሰዎች ላይ ይወርዳል፤ በዚህም ምክንያት በመካከላቸው ምስጋናና በልሳን መናገር ይኖራል። በልሳን ስንል ካልተተረጐመ በስተቀር ማንም ሊገባው በማይችል እግዚአብሔር በሰጠን ቋንቋ በመንፈስ ማምለክ ማለት ነው። በ1ኛ ቆሮ. 14 ማንበብ የምትችሉት መንፈሳዊ ስጦታ ይህ ነው። በግል ስለ መጸለይስ? ኢየሱስ ወደ ክፍላችን ገብተን በሩን እንድንዘጋ ይነግረናል። የሰማዩ አባታችን በምስጢር በጓዳችን የምንሠራውን አይቶ በአደባባይ እንደሚከፍለን ይነግረናል (ማቴ. 6፥6)። ኢየሱስ እነዚህን ቃላት ሲናገር ሊለው የፈለገው ስለ ቤት መዝጋትና መክፈት ሳይሆን ስለ አእምሮአችን ነው። ተፈላጊው ነገር ከእግዚአብሔር ጋር ብቻችንን መሆናችን ነው። አንዳንድ ሰዎች ወደ ጫካ ሲሄዱ በተሻለ ሁኔታ መጸለይ ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ ከሰዎች የተገለለ ክፍል ይፈልጋሉ። ሌሎች ደግሞ በሰዎች መካከል ሆነው ብቻቸውን መሆን ይችላሉ። ዋናው ቁም ነገር ከእግዚአብሔር ጋር ብቻችንን መሆናችን ነው። (13). በምንጸልይበት ጊዜ ወደ ክፍላችን ገብተን በሩን እንድንዘጋ ሲያዝዘን ኢየሱስ ሊያስተምረን የፈለገው ነገር ምንድን ነው? ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር መሆኑን መዘንጋት የለብንም። አንድን ሰው ልትጠይቁት ስትሄዱ እያንዳንዳችሁ የመናገር እድል ማግኘታችሁ ዋና ነገር ነው። የአንዳንድ ጊዜ ጸሎታችን የመነጋገር ዓይነት ጸሎት ሳይሆን ለእግዚአብሔር የምንሰብክ እንመስላለን። ይህ ዓይነቱ ጸሎት ደካማ ጸሎት ነው። ሰው ሊጠይቅ ሄዶ ብቻውን አውርቶ መመለስ የሚፈልግ ማን አለ? እንዲህ ዓይነት ሰዎች ቢያጋጥሙን ፈጠን ብለን እንለያቸዋለን። ከእነርሱ ጋር በማውራታችንም አንደሰትም። ጌታ አንድ ነገር ሊለን ይፈልጋል። እኛ ግን እንዲናገር እድል አንሰጠውም፤ እኛ ስንናገር ከሚሰማን ይልቅ እግዚአብሔር ሲናገረን መስማታችን ለእኛ አስፈላጊ ነገር ነው። ለመሆኑ እርሱ የማያውቀው እኛ የምንነግረው ምን ነገር አለ? ነገር ግን ስናደምጠው ልንማረው የምንችለው ለእኛ የሚሆን ብዙ ነገር አለ። እግዚአብሔርን እንዴት መስማት እንችላለን? እግዚአብሔርስ እንዴት ይናገረናል? እግዚአብሔር ሲናገር ከምንሰማበት መንገድ አንዱ ስንጸለይ የእግዚአብሔር ቃል ይዘን በመቅረብ ነው። አንድን ጥቅስ አንብበን ምን ማለት እንደሆነ ጌታ እንዲያሳየን ብንጠይቀው ትርጉሙን እግዚአብሔር ወደ አእምሮአችን ያመጣዋል። ለእኛ የሚናገረው እግዚአብሔር ነው። መንፈስ ቅዱስ አስተማሪያችን ሆኖ ወደ እውነት ሁሉ ይመራናል። መንፈስ ቅዱስ እውነትን ለእኛ እርግጠኛ ሲያደርገው በዚያን ጊዜ ስለ አስተማረን እውነት እግዚአብሔርን እናመልካለን እናመሰግናለን። እንደገና እግዚአብሔር በቃሉ እንዲናገረን ንባባችንን እንቀ ጥላለን። ለመጸለይ እንዴት ያለ አስደናቂ መንገድ ነው። (14). ስንጸልይ እግዚአብሔር የሚናገረንን የምንሰማበት ጥሩው መንገድ የቱ ነው? ኢየሱስ “በከንቱ ስለመድገም” የተናገረውን አስታውሱ (ማቴ. 6፥7)። እግዚ አብሔር የማይሰማ አይደለም። እርሱ ስለ እኛ ግድ የሌለውና ልንጎተጉተው የሚገባውም አይደለም። እርሱ የፍቅር አምላክ እስከሆነ ድረስ ልመናችንን ወደ እርሱ አቅርበን ለመልሱ በእርሱ ልንታመን ይገባናል። ልክ የመጀመሪ ያውን ጸሎታችንን እግዚአብሔር ያልሰማን ስለሚመስለን አንድን ጉዳይ ደጋግመን በማቅረብ አለማመናችንን እናሳያለን። በሌላ ጊዜ ደግሞ እግዚአብ ሔርን ማሳመን እንዳለብን እናምናለን። እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ ነው። ራስ ወዳድ ስላልሆነ ሊረዳን ይፈልጋል። (15). ትክክለኛውን ዓረፍተ ነገር የያዘውን ፊደል ክበብ። ሀ. እግዚአብሔር ጸሎታችንን መመለስ ይፈልጋል። ለ. ራስ ወዳድ ስለሆነ እግዚአብሔር አንዳንድ ጸሎታችንን አይመልስም ። ሐ. ማስረዘም ለጸሎታችን ጠቃሚ ነው። መ. እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ታምነን በድፍረትና በእምነት እንድንጸልይ ይፈልጋል። ዘወትር መጸለይ ዓላማ 4 ዘወትር የመጸለይን ፍች ማብራራት ለእግዚአብሔር ሰዎች በሙሉ ዘወትር መጸለይ እንዳለብን ተነግሮናል (ኤፌ. 6፥18)። በ1ኛ ተሰ. 5፥17 “ሳታቋርጡ ጸልዩ” የሚለውን እናነባለን። አንድ ሰው እንዴት ሳያቋርጥ መጸለይ ይችላል? እንዴትስ ዘወትር መጸለይ ይችላል? መጸለይ ከመንበርከክ በላይ መሆኑ ግልጽ ነው። ጊዜን በማሰላሰል ከማሳለፍ የአምልኮ ድርጊቶችን ከመፈጸም፣ ልመናንም ከማቅረብ ይበልጣል። ጸሎት የሁልጊዜ ተግባር ነው። ያለ ማቋረጥ የሚደረግ ነው። እንዲህ ከሆነ ደግሞ የግል ዝንባሌ ወይም የአኗኗር ዘይቤ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ዝንባሌ ወይም የአኗኗር ዘይቤ ከግልና ከጉባኤ ጸሎትና ከአምልኮ ልምምድ ውጪ ማግኘት አይቻልም። ዝንባሌዎችና ልማዶች ነገሮችን ደጋግሞ በማድረግ የሚገለጹ ናቸው። ጸሎትም እንዲሁ ነው። ጸሎትን ልምድ ካላደረጋችሁት በስተቀር ሁልጊዜ መጸለይ አትችሉም። ይሁን እንጂ ጸሎታችን መለካት ያለበት በምናሳልፈው የጊዜ ርዝመት ሳይሆን በምንጸልየው የጸሎት ጥራት መሆን አለበት። ብዙ ጊዜ አካላችን ቤተ ክርስቲያን ተቀምጦ ሃሳባችን በቤታችን ይሆናል። ወይም ጉልበታችን ለጸሎት ተንበርክኮ ሃሳባችን ማዕድ ቤት ይሆናል። በአግባቡ መጸለይ ስንማር ሁልጊዜ በአግባቡ መመላለስ እንችላለን። ዘወትር መጸለይ ማለት ይህ ነው። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከቃሉ መማር አለብን። በየዕለቱና በየሰዓቱ ለሕይወታችን ባዘጋጀላት እቅድ ውስጥ መራመድ እስክንችል ድረስ ራሳችንን ለጸሎትና ለአምልኮ ማስገዛት አለብን። (16). ጸሎትን በሚወስደው ጊዜ መለካት ትክክል የማይሆነው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ለጸሎት ምሳሌያችን ነው። እርሱ ረጅም ሰዓት በመጸለይ እንዲሁም በመጾም ያሳልፍ ነበር። ይህን የሚያደርገው ለምን ዓላማ ነበር? የልቡ ምኞት መልስ እንዲያገኝ? በደዌ የተመቱትን ነጻ ለማውጣት? በፍጹም አይደለም። ለበሽተኞች የሚያደርገው ጸሎት አጭርና ግልጽ ነበር። ለምንድን ነው እንደዚያ የሆነው? መላ ሕይወቱ የጸሎትና የአምልኮ ሕይወት ነበር። በጸሎት የአባቱን ፈቃድ በመፈለግ ሁልጊዜ በዚያ ፈቃድ ውስጥ ይመላለስ ነበር። በማንናውም ጊዜ ይጸልያል። (17). ኢየሱስ በሽተኞች እንዲፈወሱ ለምን ረዥም ጸሎት አላደረገም? እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንዴት መጸለይ እንችላለን? ኢየሱሰ በማቴ. 6፥9 እንዲህ በማለት አስተምሮናል “ስትጸለዩ እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ . . .” (ማቴ. 6፥9)። ኢየሱስ እንዴት መጸለይ እንዳለብን ሲናገር የምንጠይቃቸውን ነገሮች በምን ዓይነት ቅደም ተከተል ማቅረብ እንዳለብን መናገሩ ነው። ይህንም ሲል ከሁሉ አስቀድሞ ከሁሉም የሚበልጠውን ነገር መፈለግ አለብን። እርሱ ባስተማረው ጸሎት ውስጥ የምንጠይቃቸውን ነገሮች ቅደም ተከተል ልብ በሉ። በመጀመሪያ “ስምህ መንግሥትህና ፈቃድህ” በማለት ይናገራል። በመቀጠልም “ስጠን፣ ይቅር በለን፣ አድነን፣ አታግባን” በማለት ይጸልያል። በሌላ አባባል ኢየሱስ የሚለው በምንጸለይበት ጊዜ ለእግዚአብሔር ስም ለእግዚአብሔር መንግሥትና ለእግዚአብሔር ፈቃድ ቅድሚያ መስጠት እንዳለብን ነው። ጸሎታችንን ስጠን፣ ይቅር በለን፣ አድነን፣ ወደ ፈተና አታግባን ብለን መጀመር ትክክለኛ ያልሆነው የጸሎት ቅደም ተከተል ነው። ኢየሱስ በማቴ. 6፥33 በግልጽ እንዲህ ብሏል፡- “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግ ዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።” (18). በጸሎት ቅደም ተከተል ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የእግዚአብሔር የእግዚአብሔር እና የእግዚአብሔር ናቸው። ኢየሱስ እንዴት መጸለይ እንዳለብን ያስተማረውን ስናይ ኢየሱስ የኖረውንም ኑሮ እንማራለን። ከሁሉም በፊት የእግዚአብሔር መንግሥት ግድ የሚለን ከሆነ ሳናቋርጥ እንጸልያለን። ከእግዚአብሔር ፈቃድ ይልቅ ፍላጎቶቻችን የሚበልጡብን ከሆነ ተንበርክከን ሰዓት መቁጠር ብቻ ይሆንብናል። እግዚአብሔር በጸሎት ክፍላችን ምን ያህል ጊዜ እንደቆየን የሚቆጥርበት ሰዓት አይዝም። እግዚአብሔር በየእለቱና በየሰዓቱ የሕይወታችን ጌታ እንዲሆን ይፈልጋል። 19. አስቀድመን የእግዚአብሔርን መንግሥት ስንፈልግ እግዚአብሔር ሊያሟላ ልን ቃል የገባልን አራት ነገሮች ምንድን ናቸው? ማቴ. 6፥9-13